በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ በሚካሄደው የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ላይ የኢራን ተሳትፎ፣ አሜሪካ እና እስራኤል በሀገሪቱ ላይ የአየር ድብደባ ካደረጉ በኋላ በየካቲት ወር በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት በመባባሱ ምክንያት እርግጠኛ ሳይሆን ቆይቷል።
ኢራን በዓለም ዋንጫው ላይ እንደምትሳተፍ በቋሚነት ሲገልጹ የቆዩት የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ በምዕራብ ካናዳ በተጀመረው 76ኛው የፊፋ ኮንግረስ ላይ ለተወካዮች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ያንን አቋማቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል።
“ሌላ ነገር ማለት ለሚፈልጉ ወይም ሌላ ነገር ለመጻፍ ለሚፈልጉ ወዲያውኑ ላረጋግጥ የምፈልገው፣ በእርግጥም ኢራን በ2026 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ላይ ትሳተፋለች” ብለዋል። “እንዲሁም ኢራን ጨዋታዋን በዩናይትድ ስቴትስ እንደምታደርግ ግልጽ ሊሆን ይገባል” ሲሉ አክለዋል።
የኢንፋንቲኖ አስተያየት በቅርብ ወዳጃቸው ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋፍ አግኝቷል። ትራምፕ በኦቫል ኦፊስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢራን በመሳተፏ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ “ጂያኒ ካለው እኔ እስማማለሁ፣ ይጫወቱ” ብለዋል።
በቫንኩቨር ጉባኤ መክፈቻ ላይ ያልተገኙት የኢራን ባለስልጣናት፣ ከዚህ ቀደም የቡድናቸውን ደህንነት በተመለከተ ስጋታቸውን ገልጸው ነበር። ሀገሪቱ የምድብ ጨዋታዎቿን በሙሉ በአሜሪካ እንድታደርግ የተመደበች ቢሆንም፣ የኢራን ባለስልጣናት ጨዋታዎቹ ወደ ሜክሲኮ እንዲዛወሩ ሀሳብ አቅርበው ነበር፤ ሆኖም ይህ ጥያቄ በኢንፋንቲኖ ውድቅ ተደርጓል።
ባለፈው ሳምንት በነበረ ሌላ ክስተት፣ ጣሊያናዊው አሜሪካዊ ልዩ መልዕክተኛ ፓኦሎ ዛምፖሊ ኢራንን ጣሊያን እንድትተካ ሀሳብ አቅርበው እንደነበር ተዘግቧል። ይሁን እንጂ የአሜሪካ መንግስት ከዚህ ሀሳብ ራሱን ያራቀ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የኢራን ተጫዋቾች እንዲሳተፉ እንደሚፈቀድላቸው በድጋሚ አረጋግጠዋል። ሐሙስ ዕለት ጉባኤው ሲጀመር ከ211 አባል ሀገራት ተወካዮች መካከል ያልተገኘው የኢራን ልዑክ ብቻ ነበር፤ ይህም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከካናዳ የድንበር ባለስልጣናት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ነው።
የኢራን እግር ኳስ ፌዴሬሽን (FFIRI) ባለስልጣናት ቶሮንቶ እንደደረሱ ብዙም ሳይቆዩ ካናዳን ለቀው መውጣታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ወደ ቫንኩቨርም አልተጓዙም። የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት መህዲ ታጅ እና ሁለት ባልደረቦቻቸው በካናዳ የኢሚግሬሽን መኮንኖች “ተሰድበናል” በሚል ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
በዓለም ዋንጫው ወቅት መቀመጫቸውን በቱክሰን አሪዞና ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቁት ኢራናውያን፣ በምድብ ጂ (G) ከኒውዚላንድ፣ ቤልጂየም እና ግብፅ ጋር ተደልድለዋል። የመጀመሪያ ጨዋታቸውንም ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በሎስ አንጀለስ ከኒውዚላንድ ጋር ያደርጋሉ።
አስተያየት ይስጡን