ማንቸስተር ዩናይትድ ለካርሎስ ባሌባ 50 ሚሊዮን ፓውንድ ለማቅረብ እያሰቡበት ይገኛል። የብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮኑ አማካይ ወደ ኦልድ ትራፎርድ ሊዛወር እንደሚችል ሲነገር የቆየው ላለፉት አሥራ ሁለት ወራት ያህል ነው። ዩናይትድ ገና ተጫዋቹን መከታተል በጀመሩበት ወቅት ከ22 ዓመቱ ተጫዋች ጋር “በግል ጥቅማጥቅሞች ዙሪያ ሰፊ ስምምነት ላይ ደርሰዋል” ተብሎ ይታመናል።
ይህንን መነሻ በማድረግ ክለቡ የብራይተንን አቋም ለመፈተን የ50 ሚሊዮን ፓውንድ ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል። “ዘ አትሌቲክ” እንደዘገበው ማንቸስተር ዩናይትድ ድርድሩን ለመጀመር ያሰበው በዚህ የገንዘብ መጠን ነው።
ለባሌባ ዘንድሮው የውድድር ዘመን እጅግ ለስላሳ የሚባል አልነበረም። በብራይተኑ አሰልጣኝ ፋቢያን ሁርዘለር 15 ጊዜ ያህል ተቀይሮ እንዲወጣ ተደርጓል። ሙሉ 90 ደቂቃ መጫወት የቻለው በሦስት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ባለፈው ማክሰኞ (ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም.) ቼልሲን 3 ለ 0 በረቱበት ጨዋታ ላይ የነበረው ተሳትፎ ይገኝበታል።
ዩናይትድ ተጫዋቹን በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በቅርብ ሲከታተለው የቆየ ሲሆን፣ ባሌባ ለአገሩ ካሜሩን አምስት ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል። ካሜሩን አስተናጋጇ ሞሮኮ ጋር ተገናኝታ 2 ለ 0 ተሸንፋ ከውድድሩ እስከወጣችበት ሩብ ፍፃሜ ድረስ ለቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ነበር።
የዝውውር ዋጋው እንቅፋት ሊሆን ይችላል?
ለዩናይትድ ዋነኛው እንቅፋት ሊሆን የሚችለው የባሌባ የዝውውር ዋጋ ነው። ዩናይትድ መጀመሪያ ፍላጎቱን ሲያሳውቅ ብራይተን ተጫዋቹን ለመልቀቅ 100 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚፈልጉ በግልፅ አስታውቀው ነበር። ይህ ዋጋ ቼልሲ በ2015 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2023) ለሞይስ ካይሴዶ ከከፈለው ጋር ተመሳሳይ ነው።
ባለፈው ክረምት ዩናይትድ እስከ 75 ሚሊዮን ፓውንድ ለማውጣት ዝግጁ እንደነበር ቢታወቅም፣ አሁን ግን ከ50 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ለመክፈል ፍላጎት የላቸውም። ይህ ደግሞ በብራይተን (ሲጋልስ) ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ አነስተኛ ነው። ዩናይትድ ከባሌባ በተጨማሪ እንደ አዳም ዋርተን፣ ኤሊዮት አንደርሰን፣ ሳንድሮ ቶናሊ እና ብሩኖ ጊማሬሽ ያሉ ተጫዋቾችን ስም ከዝውውር ጋር ቢያያይዝም፣ አንዳቸውም በርካሽ ዋጋ የሚገኙ አይደሉም።
የአሰልጣኙ ሁኔታ እና የቡድኑ ግንባታ
ዩናይትድ የካሴሚሮን መልቀቅ ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ሁለት የአማካይ ተጫዋቾችን ለመቅጠር አቅዷል። ማኑኤል ኡጋርቴ ከጁቬንቱስ እና ከአያክስ የቀረበለትን ፍላጎት ተከትሎ ክለቡን የሚለቅ ከሆነ ሦስተኛ ተጫዋችም ሊያስፈልግ ይችላል።
እነዚህ የዝውውር ድርድሮች በውድድር ዘመኑ መጨረሻ በኦልድ ትራፎርድ የመሪነት መንበሩን ማን ይይዛል በሚለው ላይ ሊመሰረቱ ይችላሉ። ማይክል ካሪክ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ ዩናይትድን ከ7ኛ ደረጃ ወደ 3ኛ ከፍ ያደረገው ሲሆን፣ ክለቡ በ2018 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2026) ካሳዩት ድንቅ ብቃት አንጻር ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። ይሁን እንጂ ክለቡ ካሪክን በቋሚነት ስለመሾም ገና ውሳኔ ላይ አልደረሰም፤ ውሳኔውንም በውድድር ዘመኑ ማጠቃለያ ላይ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።
አስተያየት ይስጡን