መድፈኞቹ እሁድ ዕለት ኒውካስልን 1 ለ 0 በሆነ ጠባብ ውጤት ሲያሸንፉ፣ የቀድሞው የክሪስታል ፓላስ ኮከብ ኢዜ በ9ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ድንቅ ግብ ለድሉ በቂ ነበረች። በዚህ የውድድር ዘመን በሚኬል አርቴታ የመሰለፍ እድል ለማግኘት በትዕግስት ሲጠባበቅ የቆየው ኢዜ፣ እስካሁን በሁሉም ውድድሮች 10 ግቦችንና 3 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን (assists) ማመቻቸት ችሏል።
የአርሰናሉ አማካይ ዴክላን ራይስ ስለ ኢዜ አስደናቂ ግብ ተጠይቆ ሲመልስ፦ “እዚህ የመጣው ይህንን እንዲያደርግ ነው። ከሳምንታት በፊት እንደተናገርኩት ኳስ የመምታት ብቃቱ አስገራሚ ነው። ምን አይነት ድንቅ ተጫዋች እና ድንቅ ሰው መሰላችሁ፤ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ለእኛ በጣም አስፈላጊ ተጫዋች ይሆናል። በእርግጥም እንፈልገዋለን” ብሏል።
የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቹ ኢዜ ያስቆጠራት ግብ ለአርሰናል ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኘች ሲሆን፣ ማንቸስተር ሲቲ በኤፍ ኤ ካፕ (FA Cup) ጨዋታ ላይ በነበረበት ወቅት አርሰናል ወደ ሊጉ አናት እንዲመለስ አድርጋለች። አርሰናል ረቡዕ እለት በሻምፒዮንስ ሊግ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የሚጫወት ሲሆን፣ ቅዳሜ ደግሞ በሊጉ ፉልሃምን በሜዳው ያስተናግዳል።
ምንም እንኳን የቅርብ ጊዜ ውጤታቸው ማንቸስተር ሲቲን ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ቢመልሰውም፣ ራይስ ግን በአርሰናል መልበሻ ክፍል ውስጥ ያለው መንፈስ አዎንታዊ መሆኑን አረጋግጧል። ራይስ አክሎም፦ “ወቅቱ እስኪጠናቀቅ የምንፈልገው ይሄንን ነው፤ መሪነቱን ይዞ መቀጠልና በራስ መተማመንን ማጠናከር። አራት ጨዋታዎች ይቀሩናል፣ ሁሉንም ማሸነፍ እንፈልጋለን። ከኒውካስል የተገኘው 3 ነጥብ በጣም ትልቅ ነው” ብሏል።
አርቴታ፡ ‘ኢዜ ለእኛ ትልቅ ተጫዋች ነው’
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ስለ ኢዜ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቷል። ከድሉ በኋላ ሲናገር፦ “ኢዜ ለእኛ ትልቅ ተጫዋች ነው፣ በአሁኑ ሰዓትም በጥሩ ብቃት ላይ ይገኛል። ግቡን ለማስቆጠር አስደናቂ ክህሎት አሳይቷል። ተስፋ አደርጋለሁ ረቡዕ ዕለት ከእኛ ጋር ይሆናል” ብሏል።
አርቴታ ስለ ጨዋታው ሲቀጥልም፦ “በድሉ በጣም ደስተኛ ነኝ። ጨዋታውን ከዚህ በላይ በሰፊ የጎል ልዩነት ማጠናቀቅ ነበረብን። ውጤቱ 1 ለ 0 ሲሆን ሁልጊዜም ከባድ ነው፤ ምክንያቱም እነሱም ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች አሏቸው” ካለ በኋላ፣ ስለ ሀቨርትዝ እና ኢዜ መጠነኛ የጡንቻ ህመም (muscular niggles) ጉዳት ግን “ከባድ አይመስለንም፣ ለረቡዕ ጨዋታ መድረሳቸውን በሂደት እናያለን” ሲል ገልጿል።
አስተያየት ይስጡን