ጆሴ ሞሪንሆ በሳንቲያጎ በርናባው ዳግም የአሰልጣኝነት መንበሩን ለመያዝ ተቃርበዋል፤ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ የሪያል ማድሪድ ተመራጭ እጩ መሆናቸው ተዘግቧል።
የሪያል ማድሪድ ፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ፣ አሁን ያሉት ዋና አሰልጣኝ አልቫሮ አርቤሎዋ በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ ክለቡን ለቀው ሲወጡ የስፔኑን ግዙፍ ክለብ ወደፊት እንዲመሩ የመረጧቸው ጆሴ ሞሪንሆን ነው።
አርቤሎዋ በጥር ወር ላይ ሃላፊነቱን ከሀገሩ ልጅ ዣቢ አሎንሶ የተረከቡ ሲሆን፣ አሎንሶ በለቀቁበት ወቅት የነበረውን የላሊጋ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል። “ዘ አትሌቲክ” (The Athletic) ባወጣው ዘገባ መሠረት፣ ቀጣዩ የሪያል ማድሪድ ዋና አሰልጣኝ ማን ይሁን የሚለውን ውሳኔ በበላይነት እየመሩ ያሉት የክለቡ ፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ናቸው።
በዚህ ሂደት ውስጥ ጆሴ ሞሪንሆ የፔሬዝ ተመራጭ እጩ ሆነው ብቅ ብለዋል። ይህም የ 63 ዓመቱ አሰልጣኝ እ.ኤ.አ. በ2013 ከክለቡ ከተለዩ በኋላ ዳግም ወደ ማድሪድ የሚመለሱበትን መድረክ አመቻችቷል። ፔሬዝ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ምንም ዓይነት ዋንጫ ያላገኘው የሪያል ማድሪድ “ፕሮጀክት” ውጤታማ አለመሆን እንዳበሳጫቸው ተነግሯል፤ ጆሴ ሞሪንሆም የክለቡን ችግሮች መፍታት ይችላሉ ብለው ያምናሉ።
ይህ የሞሪንሆ የመመለስ ጉዳይ ከአንዳንድ ወገኖች ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ በፔሬዝ የሚመራው ውሳኔ ግን ውሎ አድሮ ተቃውሞዎቹን ዝም ሊያሰኛቸው ይችላል። ከዚህ ቀደም እንደተዘገበው የሞሪንሆ የዲሲፕሊን ታክቲክ፣ ያለፈው ስኬታቸው የሚፈጥረው ናፍቆት እና ተጫዋቾቻቸውን ከውጭ ትችት የመከላከል ብቃታቸው ለስፔኑ ክለብ ሳቢ አድርጓቸዋል።
ሪያል ማድሪድ የቀድሞ አሰልጣኞቹን በድጋሚ መቅጠር የተለመደ ተግባሩ ሆኗል፤ ለዚህም ዚነዲን ዚዳን እና ካርሎ አንቸሎቲ ከክለቡ ከለቀቁ በኋላ ተመልሰው መምጣታቸው እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል።
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በአሁኑ ወቅት አሁን ካሉበት ቤንፊካ ክለብ ጋር እስከ ሰኔ 2027 የሚቆይ ውል ቢኖራቸውም፣ የውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ጨዋታ ከተደረገ ከ10 ቀናት በኋላ በ 3 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ውላቸውን ማቋረጥ የሚያስችል አንቀጽ (clause) እንዳላቸው ተዘግቧል።
ሞሪንሆ በ2011-12 የውድድር ዘመን የስፔኑን ክለብ ታሪካዊ የላሊጋ ዋንጫ ድል እንዲቀዳጅ መርተዋል። ሆኖም በወቅቱ ከታላቁ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር የነበራቸው አለመግባባት ከክለቡ ለመለያየታቸው ምክንያት እንደነበር ይገመታል።
በዚያ ታሪካዊ የውድድር ዘመን ሞሪንሆ በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ የላሊጋ ጨዋታዎችን በማሸነፍ (32)፣ በሜዳቸው ውጭ ብዙ በማሸነፍ (16) እና በከፍተኛ የነጥብ ብዛት ክብረ ወሰን አስመዝግበው ነበር። ሪያል ማድሪድ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ተቀናቃኙ ባርሴሎና የላሊጋውን ዋንጫ እንዳያነሳ ተስፋ በማድረግ ከኤስፓኞል ጋር ወደ ጨዋታ ይመለሳል።
አስተያየት ይስጡን